በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡” ማር. ፲፮፥፲፭
በአውሮፓ አኅጉር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የተመሠረተው በሀገረ እንግሊዝ ሲሆን የዚህ ልዩ መንፈሳዊ ተለዕኮ ዋና ባለቤት የአሁኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በዚህ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ያስቆጠረውን የአገልግሎት ጉዞ በሰፊው ለመዳሰስ ባይቻልም መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት የሚያስችሉ ዋና ዋና የታሪክ ክስተቶችን እንደሚከለው በአጭሩ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡
የሀገረ ስብከታችን ታሪክ፣ እምነትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ የሚመነጨው በፈተና ውስጥ ካለፈ ጽኑ መሠረት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት በአውሮፓ በይፋ የተጀመረበት ታሪካዊ አጋጣሚ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የስደት ዘመን (1928-1933 ዓ.ም) ነው። ንጉሠ ነገሥቱ በለንደን እና በባዝ (Bath) ከተማ በስደት በነበሩበት ወቅት መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውንና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለመግለጽ ቀዳሚ ያደረጉት የቤተክርስቲያንን መሠረት መጣል ነበር። በዚህም መሠረት፣ በወቅቱ “ስደተኛው መድኃኔዓለም” ተብሎ የሚጠራውና የዛሬው ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ታቦት እንዲገባ በማድረግ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዳሴና ጸሎት በታላቋ ብሪታንያ ምድር ተከናወነ። ይህ ታላቅ ክስተት ቤተክርስቲያናችን ኩላዊነት እና ከሀገር ወሰን በላይ የምትሰበክ ሕያው እምነት መሆኗን የመሰከረ ግልጽ ማስረጃ ነው። ሀገረ ስብከታችንም በታሪክ አጋጣሚ የአገልግሎት መስክ ብቻ ሳይሆን፣ የእምነት መጠጊያና የሐዋርያዊ ተልዕኮ ተስፋ መሆኗን የሚያሳይ ታሪካዊና መንፈሳዊ አሻራን በሀገሪቷ ላይ ጥሏል።
በአውሮፓ ምድር የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት። ይህች ታሪካዊት ደብር መሠረቷ የተጣለው በ1964-1965 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን፣ ምስረታዋም በወቅቱ የነበሩት የካሪቢያንና የአፍሪካ ተወላጆች መንፈሳዊ ጥማት ምላሽ እንዲያገኝ በቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድና ሐዋርያዊ መመሪያ ነበር። ይህንን ተከትሎ በ1966 ዓ.ም አባ አረጋዊ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ) የደብሩ አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በታላቅ ትጋት አገልግለዋል። ይህ ዘመን ቤተክርስቲያኗ በስደትና በእንግድነት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብቸኛ የጸሎትና የማኅበራዊ መገናኛ ማዕከል በመሆን ያገለገለችበት ወቅት ነበር።

የምዕመናን ቁጥር እየጨመረና የአጥቢያዎች መስፋፋት እየታየ በመምጣቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የአውሮፓን አገልግሎት በበላይነት የሚመራ መዋቅር መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ አገኘው። በዚህም መሠረት፦
❖ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፡ በ1985 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ጵጵስናን ተቀብለው፣ የመጀመርያው የአውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመደቡ። መንበረ ጵጵስናቸውን በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን በማድረግ፣ ቤተክርስቲያኗ በምዕራቡ ዓለም መዋቅራዊ ቅርጽ እንድትይዝ እስከ እረፍታቸው ድረስ በቅድስና አገልግለዋል።
❖ ከብፁዕነታቸው እረፍት በኋላ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ሙሴ በተለያዩ ጊዜያት መንበረ ጵጵስናቸውን ለንደን ላይ በማድረግ፣ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የወንጌልን ዘር ዘርተዋል።
❖ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፡ በመቀጠልም የአውሮፓ አህጉረ ስብከት በድጋሚ ሲደራጅ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለስምንት ዓመታት በታላቅ ትጋት አገልግለዋል። በዚህም ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ በርካታ አጥቢያዎች እንዲተከሉ አድርገዋል።

የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር ለሁለት ተከፍሎ በቆየችባቸው ዓመታት ውስጥ በአውሮፓ የሚገኙ አጥቢያዎችም የዚያ ስብራት ሰለባ ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም ግን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነትና በቅዱሳን አባቶች ጥረት በ2011 ዓ.ም የታሪካዊው ዕርቀ ሰላም መደረግን ተከትሎ፣ አውሮፓ በአራት አህጉረ ስብከት ተደራጀ። በዚህም “የዩናይትድ ኪንግደም እና የአየርላንድ ሀገረ ስብከት” የሚለውን ራሱን የቻለ ስያሜና መዋቅር አገኘ።
በዚህ አዲስ መዋቅር የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ በመሆን የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ነበሩ። ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱን በተቋማዊ ደረጃ ለማደራጀትና ጠንካራ መሠረት ለመጣል ሰፊ ዕቅድ የነበራቸው ቢሆንም፣ ባልታሰበ ሁኔታ በሞተ ዕረፍት በመለየታቸው የጀመሩት ሥራ ለተተኪው አባት ተላልፏል።

በ2013 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መድቧል። ብፁዕነታቸው ቀደም ሲል በውጪው ዓለም ለረዥም ዘመናት ሲያገለግሉ የኖሩ በመሆናቸውና ለዓለም አቀፍ ነገረ መለኮታዊ ውይይቶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይመላለሱ ስለነበር፣ የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት ጠንቅቀው የሚያውቁ አባት ናቸው። ብፁዕነታቸው ሐዋርያዊ ኃላፊነቱን ሲረከቡ የተመለከቱት ክፍተት፣ ሀገረ ስብከቱ ለረጅም ዓመታት ቢቆይም ራሱን የቻለ “ቋሚ መንበረ ጵጵስና (ጽሕፈት ቤት)” እና ለአባቶች ማረፊያ የሚሆን ሕንጻ አለመኖሩን ነው። ይህንን ተቋማዊ ድክመት ለመቅረፍ ካከናወኗቸው ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው።
❖ ሕጋዊ ሰውነትና ምዝገባ (Charity Commission): ሀገረ ስብከቱ ከተመሠረተ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳን ሕጋዊ ሰውነት ያለው ስላልነበረ ይህንኑ ችግር በመገንዘብ በሀገሪቱ ሕግ የታወቀ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርገዋል። ይህም ቤተክርስቲያኗ በራሷ ስም ንብረት እንድታፈራና የሕግ ከለላ እንድታገኝ አስችሏል።
❖ ቃለ አዋዲንና የሀገሪቱን ሕግ ማጣጣም: የቤተክርስቲያናችንን ቀኖናዊ ሕግ (ቃለ አዋዲ) ከሀገሪቱ የፋይናንስ፣ የአስተዳደርና የንብረት አያያዝ ሕግጋት ጋር በማጣጣም ጠንካራ መመሪያ አዘጋጅተዋል። ይህም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር መንገድ ከፍቷል።
❖ ጥበቃና ደኅንነት (Safeguarding): ለሕፃናትና ለአረጋውያን ልዩ ጥበቃ የሚያደርግ ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቤተክርስቲያኗ ለሁሉም ተገልጋዮች አስተማማኝ መጠጊያ እንድትሆን አድርገዋል።

ምንም እንኳን ሀገረ ስብከቱ በታሪክ ቀዳሚ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ቋሚ የሆነ የመንበረ ጵጵስና ሕንጻና ጽሕፈት ቤት አለመኖሩ የአገልግሎቱን ቀጣይነት ፈታኝ ያደርገዋል። ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ለሀገረ ስብከቱ የሚመጥን ቋሚ ማዕከል ለመግዛት ሰፊ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ አገልግሎት በሀገረስብከቱ ያለውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በጥራት እና በስፋት ለማከናወን እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን በማስጠበቅ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ በዘመናችን ለትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ ቅርስ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ከብጹዕ አባትቻን ጎን በመቆም ይህንን ተቋማዊ ራዕይ ከፍጻሜ ለማድረ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።

